ECADEF – ሲሞላልኝ በሳምንት ካልሆነልኝ ደግሞ በአስራ አምስቱ ሰላምታዬን ካሉበት የማደርሳቸው ወዳጆች አሉኝ። ለአገር ምድሩ ሳይሆን በጣት የሚቆጠሩ። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሙያ ባልደረባዬ ኤልያስ ወንድሙ ነው። ትውውቃችን የመንገድ ላይ አይደለም። የኔዎቹ የነፃ ፕሬስ አባላትና የሃገሬ ሰላም ወዳድ ኃይሎች በግፈኞቹ የሕወሃት አባላትና ሹመኞች የሚሰደዱበት የሚታሰሩበት ብሎም የግፍ ፅዋ የሚቃመሱበት በእነዚያ የትግል፣ የፈተናና የፍልምያ ዓመታት የልብ ወዳጅና ለእውነት የቆሙ በመብራት በሚፈለጉበት የወያኔ የግፍ ዘመናት። ዛሬም ይህ ሐቅ ገሃድ ነው።
የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማህበር (ኢነጋማ) በአለም አቀፍ “የመጻፍ ነጻነት (Freedem to write) ሽልማት መሰጠቱንና ከመላው አለም ከሚገኙ የጋዜጠኞች ማህበራት ጋር እንደሚወዳደር በቀጭኑ ሽቦ ዜናውን ያበሰረኝ ኤልያስ ነበር። የአይበገሬዎቹን የነፃ ፕሬስ አባላት ተጋድሎና የማህበራቸውን ፋና ወጊነት፣ ለተሰየሙ ዳኞች በማስረዳትና በመሟገት ኢነጋማን ለ12ኛው ዓለም አቀፍ ሽልማት ያበቃ ትጉህ ጋዜጠኛ ነው። እናም ኤልያስ ከጥቂት ወራት በኋላ የምስራቹን አበሰረኝ፤ እኔና ኤልያስም ሎስ አንጀለስ ላይ ለዓይነ ሥጋ በቃን። እንዲህ እንዲህ እያልን ከዘመን ዘመን ተሻገግረን ሥደት የሚሉት ጣጣ ደግሞ ጊዜውን ጠብቆ ዳግመኛ አገናኘን።
መንፈሰ ጠንካራዋን፣ በአራአያነቷ ጭምር ልትደነቅና ልትከበር የተገባትን ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል በተሸለመችበት ታላቅ ሥነ ሥርዓት ላይ ዋሽንግተን ዲሲና ሎስ አንጀለስ ሥነ ሥረዓት ላይ ዳግም ተገናኘን። ለእነዚህ ሁለት ከፍተኛና ታሪካዊ ሽልማቶች የኤልያስ ውንድሙን ወደር የለሽ አስተዋፅኦ የዕድሜ ድሃ ካልሆንኩ ወደፊት እጽፈዋለሁ።
ሌላም አለኝ። አስቸጋሪዎን ውጣ ውረድና ውስብስቡን ቋጠሮ ከመዘርዘር ለጊዜው ልቆጠብ ግን እወዳለሁ። በትግሉ የመጀመሪያ ረድፍ ተሰልፎ ከፍተኛ ተጋድሎ በማድረጉ የምኮራበት የሙያ ባልደረባዬና ሕይወት ለመታደግና ከወያኔ መንጋጋ ፈልቅቆ ለማውጣት ብሎም የነፃ ፕሬስ ተሟጋችነቱንም በዓለም አደባባይ ለመመስከር ያስቻለን ሽልማት በማስገኘት ረገድ የኤልያስ ድርሻ እጅግ ብዙ ነው። ምሥጋናዬን አሁንም ካለበት ትድረስልኝ።
የሕይወት ታሪክ እየጻፍኩ አይደለም። በቅርቡ ለህትመት በበቃው የሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም መፅሃፍ ምክንያት በኤልያስና አሳታሚ ድርጀቱ ላይ የተቃጣው ጥቃት አሳዝኖኝ ትንሽ ለማለት ነው።
የፀሐይ አሳታሚ ድርጅት በአንድ ትጉህ ባለሞያና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት በሃገራችንም እንዲከበር በሚጣጣር ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነው የሚመራው። ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ለንባብ ካበቃቸው አያሌ መጽሐፍት መካከል ይበልጡ ኢትዮጵያዊ ገጽታ የተላበሱ በመሆናቸው በበኩሌ እንደ ሃገርና ትውልድ ቅርስ እቆጥራቸዋለሁ። በተለይም ለወጣቱና ለመጪው ትውልድ። እናም እንደተቀሩት ሁሉ የሌ/ኮሎኔል መንግሥቱን መጽሐፍ በፀሐይ አሳታሚ ቢቀርብ ሐጢአቱ ምኑ ላይ ነው? በሕይወት ያሉ የሥርዓቱ ባለሟሎችም ሆኑ የታሪክ ምሑራን እንዲያም ሲል ዓቅምና ብቃት የታደሉ ፀሐፍት በሚስማሙበትም ሆነ በማይስማሙባቸው የኮሎኔሉ ጽሑፎች ላይ የየበኩላቸውን በማለት ፍርዱን ለአንባብያን መተው አይገባምን? ይህ ደግሞ ማንም ለማንም የሚሰጠው አልያም የሚነፍገው መብት እስካልሆነ ድረስ ቂም ቋጥሮ መነሳትና አሳታሚውን ለጉዳት መዳረግስ ይገባል? እንደሌሎቹ ሁሉ የማከብረው ድህረ-ገጽ ልምን ይህን ርምጃ ወሰደ?
የሙያ ባልደረባየ የነበረችው ጋዜጠኛ ገነት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ከኮሎኔል መንግሥቱ ጋር ያደረጋቸውን ቃለ ምልልስ አንብቤያለሁ። ያኔ ታዲያ በሜጋ አሳታሚ ላይ የደረሰ ወቀሳ ስለመኖሩ አላየሁም፤ አልሰማሁምም። ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዲከበርና የፕሬስ ነፃነት ያብብ ዘንድ የሚሟገቱ ወገኖች የጣፋጩ ፍሬ ተቋዳሾች እነርሱ ራሳቸው ብቻ እንዲሆኑ አይደለም። ንፉጎችና የሰብዓዊ መብት ባላንጣዎችም እንዲጋሩት እንጂ። የዲሞክራቲክ ኃይሎች የሚታገሉትም ለቄሳሩ ዘመን “ዓይን ያጠፋ፡ ዓይኑ ይጥፋ” ሥርዓት ተመልሶ መምጣት አይደለምና! ሲኦን ሲሆን ለባለጋራ የሚወረወር ጦር ወንድምን እንዳ..ጥል አሰባበቅም ላይ ሆነ አሰነዛዘር ላይ መጠንቀቁ ብልህነት ይመስለኛል።
ኢትዮጵያዊው ፀሐይ አሳታሚ እንደ ንግድ ተቋም ብቻ ተቆጥሮ ገሸሽ ሊደረግ አይገባም። የፕሬስ ነፃነት ተሟጋቾችም እውነትንና የቆሙለትን ዓላማ የሚፈትን ክስተት ሲፈጠር ግንባራቸውን እንጅ ጀርባቸው ሊሰጡ አይቻላቸውም። በወዳጅነታችን እንሰንብት!
SOURCE: ክፍሌ ሙላት – ECADForum