የቅጂ መብቶች እና የቅጂ ወንጀሎች!

የአእምሮ ውጤቶች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች

አንድ ሰው የሌላን ሰው ቤት ቢያቃጥል ወይንም ጉዳት ቢያደርስ በየትኛውም ሀገር ውስጥ ባሉ ህግጋት ንብረት በማውደም ወንጀል ተጠያቂ ይሆናል። አንድ መጸሀፍ መደብር ገብቶ በሺህዎች የሚቆጠሩ መጻህፍትን በመዝረፍ ለመንገደኛ ሁሉ የሚያድል ቢኖር ይህም በንብረት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሆኖ ይቆጠራል። የመጽሀፍ ቅጂ መብትን (ኮፒ ራይት) ጥሶ መጽሀፉንም በመቃኛ ቃኝቶ (እስካን) በዘመኑ ቴክኒዮሎጂ በድረ ገጽ ላይ የሚያወጣ ምን ይባላል? ይህስ አስከፊ የወንጀል ተግባር አይሆንምን? ህሊና ቢስ እኩይ ምግባርስ አያስብልምን?

ለመሆኑ እንዲህ ያለው ተግባር አግባብ ይሆን?

አሳታሚ፣ ጸሀፊ ወይንም አንድ አርቲስት መጸሀፍ ቢያሳትም፤ ሙዚቃ ቢደርስ፣ ስእል ቢነድፍ ወይንም ሌላ ተመሳሳይ የአእምሮ ጭማቂ ውጤቶችን ቢያቀርብ እሱ/ሷ ያቀረቡት የአእምሮ ውጤት ህጋዊ ተቀባይነት እንዳለው እንደማንኛውም ጠቃሚ ንብረት ሁሉ ህጋዊ ከለላና እውቅና አለው።

ዶክተሮች፣ የህግ ባለሙያዎች፣ ኢንጅነሮች ወይንም ሌሎች በሙያቸው ውጤት እንደሚከበሩ በስነጽሁፍ፣ በስነ ጥበብ ወይንም በህትመት ሙያ የተሰማሩ ህይወታቸውን የሚመሩት የአእምሮ ውጤቶቻቸውን ለህዝብ በማቅረብ ነው።

ይሁንና ኢትዮጵያዊያን ሙዚቀኞች ከያንያን (አርቲስት) እና ጸሀፍት የደከሙባቸውን የአእምሮ ውጤቶቻቸውን አክብሮት በመንሳትና በባለመብተትነታቸው ላይ በማሴር ረገድ በአንዳንድ ግለሰቦች ላይ የሚስተዋለው እኩይ ተግባር ውስጥን የሚያሳምም ብቻም ሳይሆን የሚያሳብድም ሆኖ ይገኛል።

ሥመ ጥር የኢትዮጵያ ሙዚቀኞችን ስራዎች ለምሳሌ የጥላሁን ገሰሰ፣ ማህሙድ አህመድ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ አለማየሁ እሸቴ፣ ኪሮስ አለማየሁ፣ ካሳ ተሰማ፣ ከተማ መኮነን፣ አስናቀች ወርቁ፣ ሜሪ አርምዴ፣ ሂሩት በቀለ፣ አሊ ቢራ፣ አስቴር አወቀ፣ ኩኩ ሰብስቤ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ቴዎድሮስ (ቴዲ አፍሮ) ካሳሁን፣ ሻምበል በላይነህንና እንዲሁም የሌሎች በርካታ አርቲስቶች ሙዚቃዎችን ጨምሮ በሆነ መንገድ በየድረ ገጾች ላይ ተከማችተው የፈለገ እንደፈለገው በነጻ እያወጣ ይኮመኩማቸዋል። ይዝናናባቸዋል።

አርቲስቶቹ ግና አምስት ሳንቲም እንኳን አይከፈላቸውም። ስራዎቻቸውም ከእነሱ ፈቃድና ይሁንታ ውጭ ነው የሚሰራጩት። ለሙዚቃ ወንበዴዎች ግን የገቢ ምንጫቸው ነው። ዝርፊያቸው በድረ ገጾቻቸው በሚወጡ ማስታወቂዎች፣ በሰብስክሪብሽን አልያም በሌላ መልክ የማያቋርጥ ገቢ ያገኙበታልና።

ሙዚቃዎችን ከህግ ውጭ በኮምፒውተር መጋዚኖቻቸው የሚያከማቹትም ሆኑ ወይም ከእኒህ ህገ ወጦች በህገ ወጥ መንገድ ወደራሳቸው የኮምፒውተር መጋዘን የሚያወርዱት ሁለቱም ታላላቅ ጠቢባን ሙያተኞችን ለማደህየት ብቻ ሳይሆን የሚሰሩት፤ ሙያተኞቹ ባህልን ለማሳደግና ፈጠራን ለማጎልበት የሚያደርጉትንም ድካም በተባበረ ክንዳቸው የሚደቁሱ/የሚያወድሙ ሆነውም ይገኛሉ።

በፕሬሱ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች?

ይህ ዘግናኝ አስነዋሪ የ’ኦን ላይን’ ውንብድና ባህል ሰሞኑን ወደ ከፍተኛው የዝቅጠት ምእራፍ ተሸጋግሮ የአለም አቀፉን እና የሀገራዊ የቅጅ መብት /ኮፒ ራይት/ ህግጋትን በጠራራ ፀሐይ በመጣስ አንድ ድፍን መጽሀፍን በመቃኛ (እስካን) ተቃኝቶ በድረ ገጽ ላይ ተለጥፎ ወጥቷል። ይህ መጽሐፍም በቅርቡ የታተመው የኢትዮጵያ ወታደራዊ አምባገነን መሪ ነበረው የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማሪያም ትውስታ /ማስታወሻ/ መጽሀፍ ነው።

ይህንን ተግባር የፈጸመው ድረ ገጽም ድርጊቱ ትክክለኛ ስለመሆኑም የሚከተሉትን ምክንያቶች ደርድሯል።

“በሀራሬ ዚምባቡዌ በስደት ላይ የሚኖረው ህዝብ ጨራሹ ፣ አረመኔው አምባገነን መንግስቱ ኃይለማሪያም ከአምስት መቶ ገጾች በላይ ያዘለ መጽሀፍ የጻፈ ሲሆን ይህም ሎስ አንጀለስ በሚገኘው ፀሐይ አሳታሚ ድርጅት ታትሟል።

ይህ ዘግናኝ ወንጀለኛና የቀይ ሽብር እልቂት ቀንደኛ ለዚህ ተግባሩ አንዳችም ጸጸት የማይሰማው ሲሆን ለፍርድም ያልቀረበ ጨፍጫፊ ነው። ሐሰት ከተሞላው ከዚህ የመጸሀፍ ሽያጭም የሚያጋብሰውን ትርፍ እየጠበቀ ይገኛል። በበኩላችን ይህ ወንጀለኛ ለፈጸመው ወንጀል በህግ ፊት ቀርቦ መቀጣት ያለበትና መጽሀፉንም በመሸጥ ከሚያገኘው ትርፍ መታገድ ያለበት ነው ብለን እናምናለን። በመሆኑም ማንኛውም ፍላጎት ያለው አንባቢ በነጻ መጽሀፉን አግኝቶ እንዲያነብ በፒ.ዲ.ኤፍ አራብተን በኢንተርኔት ለቀናል።”

የዚህ ድረ ገጽ አዘጋጆች ይህ ህገ ወጥ የሆነው የማራባትና የመለጠፍ ተግባራቸው ህጋዊ መሆኑንና በአሜሪካ ህግ መሰረትም መብት እንዳላቸው ጽፈዋል።

“የወሰድነው እርምጃ አሜሪካን ውስጥ በሚገኘው “ሰን ኦፍ ሳም” (son of sam) ህግ መሰረት የተደገፈ ነው። ይህም ህግ ወንጀለኞች የወንጀል ታሪካቸውን ለአሳታሚዎች በመሸጥ ትርፍ እንዳያጋብሱ ያግዳል። ህጉ ለእኒህ ወንጀለኞች ተባባሪ የሚሆኑትንም ሁሉ የሚያግድ ነው። እንደ አስፈላጊነቱም የሚለጠጠው ህግ ከወንጀለኞቹ ባሻገር ጓደኞቻቸውን፣ ጎረቤቶቻቸውንና፣ የቤተሰቦቻቸውን አባላትም ያግዳል። በብዙ ሀገሮች የጅምላ ፍጅት ፈጻሚነትን መካድ ወንጀል ነው። መንግስቱ ቀይ ሽብርንና የጅምላ ፍጅትን አጥብቆ የካደ ነው። ጉዳዩ ያብከነከናቸው ኢትዮጵያዊያን መሰረቱን ሎስ አንጀለስ ባደረገው አሳታሚ ድርጅት እና በመንግስቱ ላይ ህጋዊ ክስ የሚመሰረትበትን ሁኔታዎች እየመረመሩ ይገኛሉ። አሳታሚ ድርጅቱም ለዚህ ተግባሩ ቅጣት በሁሉም ኢትዮጵያዊያን በኩል አድማ እንደሚደረግበት ይገመታል። ወንጀለኞችና ጅምላ ጨፍጫፊዎች የሚጽፉትን በሀሰት የተሞላ መጸሀፋቸውን ማሳተምና ትርፍ እንዲያጋብሱ ማድረግም ራሱ ወንጀል ነውና።”

ህገ ወጥ ለሆነው ልጠፋ (ፖስቲንግ) መነሳሻው መንግስቱ ‘ከመጸሀፉ ሽያጭ የሚያገኘው ትርፍ ለማገድ’ የሚል ነው። እንዲህ ያለው ድርጊት ግን ‘በሀሰት የታጀለ መጸሀፍ’ የሚሉትን በስፋት እንዲሰራጭ ጥርጊያውን የሚያደላድል ነው።

ይሁንና እኒህ የኮፒ መብትን ህግ ጣሾች መጽሀፉን በኦን ላይን ላይ ሁሉም እንዲያነበው በመለጠፋቸው መንግስቱ በእነሱ ላይ የሰነዘረውን ተአማኒነት ከማሳጣት ይልቅ ራሳቸውን ተአማኒነት አሳጥቷቸዋል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ዋናው የበቀል ኢላማ ሆኖ የሚገኘው አሳታሚው፣ ጸሀይ አሳታሚ እንጂ መንግስቱ አይደለም። የቅጅ መብት ጣሾቹ የተውገረገረ መልእክት ግን ግልጽ ነው፤ በአንድ መጽሀፍ ውስጥ የሚገኘው መልእክት ካልተዋጠላቸው በቀላቸውን የሚወጡት አሳታሚ ድርጅቲን ለማክሰር መጽሀፉን በመቃኛ ቃኝቶ በኦንላይን መበተን።

መንግስቱ ባቀረበው መጽሀፍ ውስጥ ባሉ እውነቶች ወይም ሀሰቶች አለመስማማት አንድ ነገር ነው። መጽሀፉን ያነበብኩት በመሆኑ መንግስቱ እየመረጠ ያቀረባቸው ‘እውነቶች’ ትክክለኛ ስለመሆናቸው እጠራጠራለሁ። ስለ ሰላማዊ መብቶች ጥሰቶቹም በግሉም ሆነ በአገዛዙ ስም ሀላፊነትን ከመውሰድ ራሱን የማግለል ጥረቱንም እቃወማለሁ። ይሁንና እንዲህ ያለው ባህሪ የአምባገነኖች ሁሉ መለያ ነው። ሁሉም ታሪካቸውን ሲጠርቁ ወንጀሎቻቸውን እንደ አርበኛነት ገድል ታሪካቸውንም እንደ ሰማእት አድርገው ነውና።

ምንም እንኳን መንግስቱ ያቀረቧቸውን በርካታ ‘እውነቶች’ የማልስማማባቸውና የሰበአዊ መብቶችን አያያዙንም ያለአንዳች ገደብ የማወግዘው ቢሆንም፤ መንግስቱ መጽሀፍ የመጻፍ (በውሸት የተሞላም ቢሆን) እና የማሳተም መብቱን በግንባር ቀደምትነት ቆመው ከሚሟገቱለት የመጀመሪያው እኔ እሆናለሁ። መንግስቱ በነጻነት ሀሳቡን የመግለጽ መብቱን በእርግጥ እከላከልለታለሁ። በሴፕቴምበር 2010 ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ መንግስቱን የተካው መለስ ዜናዊ የመናገር ነጻነቱ እንዲጠበቅ እንደተከላከልኩት ሁሉ። ለምንድነው እኒህ ሁለት አምባገነኖች ራሳቸውን መግለጽ የማይፈቀድላቸው? የእነሱን ‘እውነቶች’፣ ‘ሀሰቶች’፤ አስተሳሰባቸውን ወይም አስተያየታቸውን የሚፈራው ማን ነው? ህዝቡ እኒህ አምባገነኖች የሚሉትን ሰምቶ የራሱን ብያኔ የመስጠት መብት የለውምን?

የአለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች አዋጅ አንቀጽ 19 እንዲህ ይላል፦ ‘ማንኛውም ሰው ሀሳቡን በነጻነት የመግለጽ መብት አለው። በዚህ የሀሳብ ነጻነት መብትም ማንኛውንም አይነት መረጃ እና ሀሳብ ያለ አንዳች ተጽእኖና  የድንበር /የጂኦግራፊ/ ገደብ በማንኛውም የሚድያ አይነት ማሰራጨትና መቀበል ይችላል።”

“ሁሉም” የሚለው ቃል እምባገነኖችንና የሰበአዊ መብቶችን ረጋጮችንም ያጠቃለለ ነው። ለሰላም፤ ለዲሞክራሲ እና ለሰበአዊ መብቶች ቆመናል የምንል ሁሉ የአምባገነኖችን አረመኔአዊነት፣ ቅጥፈትና አየር ወለድ ፈጠራ በማንኛውም አጋጣሚ ሁሉ የማጋለጥ የሞራል ግዴታ አለብን።

የአምባገነኖችን አስተሳሰብ ወይም አመለካከት ባፈንን ቁጥር በቅጥፈታቸው ላይ ያለንን የሞራል የበላይነት ማኮሰሳችን ብቻም ሳይሆን ከእነሱ ያልተሻልን የእነሱ ግልገሎች መሆናችንንም ጭምር ነው ለአለም የምናውጀው። “የምናወግዛቸው ወይንም የምንቃወማቸው ሰዎች ሀሳባቸውን በነጻ የመግለጽ መብታቸውን የማንቀበል ወይንም የማናምን ከሆነ ከቶም በሀሳብ ነጻነት አናምንም ማለት ነው።”

የመንግስቱን መጽሀፍ በኦን ላይን ላይ የለቀቁት የህግ ተጻራሪ ሆነውም ነው የቆሙት። መጸሀፉን የመለጠፍ መብት ሰጥቶናል የሚሉት የ ‘ሰን ኦፍ ሳም ህግ” በ1983 (እአአ) ነበር በኒው ዮርክ ስቴት ውስጥ የጸደቀው።

ይህ የ’ሰን ኦፍ ሳም ህግ’ ፍርድ ያገኙ ወይንም ፍርድ የተሰጣቸው ወንጀለኞች የወንጀል ታሪካቸውን ለአሳታሚዎች በመሸጥ የገቢ ምንጭ እንዳይሆናቸው ለማገድ የተደነገገ ነው።

በ1991 (እአአ) የአሜሪካን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይህ የ’ሰን ኦፍ ሳም ህግ’ ህገ መንገስታዊ አይደለም በማለት ውድቅ አድርጎታል።በ2001 (እአአ) ኒው ዮርክ ውስጥ በጸደቀው ደንብ መሰረት ህጋዊ ፍርድ የተሰጠው ወንጀለኛ የተወሰነ የገንዘብ መጠን ማግኘት ሲጀምር የወንጀለኛው ሰለባ የሆኑት አካላት እንዲያውቁት ማድረግ የሚል ይገኝበታል፦ ከሌሎች ጉዳዮች በተጨማሪ። ተመሳሳይ ህግ በ2002 (እአአ) ካሊፎርንያ ውስጥ በሚገኘው የስቴት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደርጓል።

በፌደራል ህግ (18 U.S.C & 3681 (2000) [Special Forfeiture of Collateral Profits of Crime]) መሰረት የዩ.ኤስ አቃቢ ህገ ወጥ ወንጀለኞች ከወንጀል ተግባራቸው ጋር በተያያዘ ኮንትራት፣ በሲኒማ፣ በመጸሀፍ በጋዜጣ፣ በመጽሔት፣ በራዲዮ ወይንም በቴሌቪዥን … ስርጭቶች አማካይነት ያገኙትን ገቢ በከፊል ወይንም በሙሉ በፍርድ ቤት ማዘዣ ለማሳገድ ይቻላል።

በተባበረው የአሜሪካን መንግስት ህግ ውስጥ ለግለሰቦች ወይንም ቡድኖች የተፈቀደ ህዝብ ፈጆችን አድኖ የመያዝ ወይንም በቅጥፈት የተሞላ ታሪካቸውን የያዘ መጽሀፋቸውን በኦንላይን በመበተን ትርፍ እንዳያገኙ የማገድ ወይንም የደም ገንዘብ ከማግኘት ለማቀብ በሚል ሰበብ የአሳታሚዎችን የቅጂ መብት (ኮፒ ራይት) ህግ የመጣስ ልዩ ‘የህግ አስፈጻሚነት’ ሀይል ለማንኛውም (ግለሰቦችም ይሁኑ ቡድኖች) ከቶም አልሰጣቸውም።

ከህግ አንጻር የየትኛውም ስቴት ወይንም ፌደራላዊ ፍርድ ቤት መንግስቱ ኃይለማሪያም ከመጸሀፉ ሽያጭ የሚያገኘውን ‘ትርፍ’ የማገድ ህጋዊ ስልጣን ለውም። እንዲህ ያለ የህግ ተፈጻሚነት ሊኖር እንኳ የሚችለውም መንግስቱ በህግ ፊት ቀርቦ ህጋዊው የፍርድ ሂደት ሁሉ ከተሟላ በኋላ ብቻ ነው የሚሆነው።

አዎ አምባገነኖችም ቢሆኑ የመኖር መብታቸውንና ነጻነታቸውን፣ ንብረታቸውን ሊያጡ የሚችሉት ሙሉ ህጋዊ መብታቸው በህግ ፊት ከተጠበቀላቸው በኋላ ነው።

በቅጅ መብት ህግጋት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች

ህገ ወጥ የሆነው የመንግስቱ መጸሀፍ ልጠፋ ስለ ሀሰቶቹ፣ ስለእውነቶቹ ወይንም ወንጀለኞች ከወንጀላቸው ትርፍ ስለማግኘታቸው አይደለም፤ የቅጅ መብትን ህግ ስለመጣስ ወንጀልነቱ እንጂ። ከ1886 (እአአ) ጀምሮ የስነ ጽሁፍና የስነ ጥበብ ስራዎችን ለመጠበቅ በወጣው የበርኒ ጉባኤ (አርቲክል 2ትን ይመልከቱ) የስነ ጽሁፍና ስነ ጥበብ ስራዎችን የመጠበቂያ ድንጋጌዎችን አስቀምጧል። በቁጥር 17 u.s.c 506 (a) (1) (b) የሚከተለው ድንጋጌ ይገኛል። “ማንኛውም ሰው ይሁን ብሎ የቅጅ መብትን ህግ ከጣሰ በክፍል 2319 ስር በ18ኛው ደንብ መሰረት ይቀጣል። ይህ የቅጅ መብት ህግ ጥሰት የተከናወነውም…(b) በ180 ቀናት ጊዜ ውስጥ በማንኛው ቀን የገበያ ድምር ዋጋው ከ1000 ዶላር በሆነ የፎኖሪኮርዶች አንድ ወይም ከዚያ በላይ ቅጅዎችን  ወይንም አንድ አልያም ከዚያ በላይ የሆኑ የቅጅ መብታቸው የተጠበቀ ስራዎችን በሚያራባ፣ በሚያሰራጭ፣ ይህ በኤሌክትሮኒክስ መጠቀምንም ያካትታል። በማንኛውም ህግ ተላላፊ ላይ /የቅጣት ደንቡ/ ተፈጻሚ ይሆናል።

የቅጂ መብት ህግ ዋናው አላማ የአእምሮ ጭማቂ ውጤት የሆነን /ኦሪጂናል/ ስራ የአእምሮ ውጤት ባለቤትነት መብትን እስከተወሰነ የጊዜ ሰሌዳ ድረስ ለማስጠበቅ ነው። በዩ.ኤስ. አሜሪካ ይህ የጊዜ ሰሌዳም የጸሐፊው /ደራሲው/ የህይወት ዘመንና ከዚያ በኋላ ላሉት ተከታታይ 70 ዓመታትን ጨምሮ ይሆናል።

በኒህ ህጋዊ ዓመታት ውስጥም የቅጂ መብት ባለቤት የሆነ የቅጂ መበት ያለውን ስራ እንደገና የማራባት፣ የማሰራጨት፣ የማስተዋወቅ፣ የመፍቀድ እና ከዋናው ስራ የተቀዱ ተዛማች ስራዎችን የማዘጋጀት መብት አለው። ይሁን እንጂ በተወሰነ ወይንም በተገደበ ደረጃ ሌሎች ሂሳዊ አስተያየት ለማቅረብ ወይንም ዜና ለማጠናቀር ወይንም ለማስተማሪያ፣ ለስኮላርሺፕ አልያም ለምርምር ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ የ’የአግባባዊ አጠቃቀም’ ደንብ ጨምሮ ያትታል።

በባህል ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች

ስለ ጸሀይ አሳታሚዎችና ይህንን ድርጅት ከመመስረት አንስቶ እስከማጎልበት ድረስ ሌት ተቀን ለዓመታት ስለዳከረው ወጣት፤ የዚህ ወጣት ያልተገደበ ጥረት ውጤት የሆነው ፀሐይ አሳታሚዎች በኢትዮጵያና እንዲሁም በክፍለ ዓለሙ በአፍሪካ ላይ ለሚጽፉ ኢትዮጵያዊያንና አፍሪካዊያን ምሁራንና ተመራማሪዎች ስራዎቻቸውን ለህዝብ በማቅረብ አኳያ በማበርከት ላይ ስላለውም ሚና የማያውቁ ጥቂት የህብረተሰብ ክፍሎች ያሉ ይመስለኛል።

ኤልያስ ወንድሙ በ1998 (እአአ) ነበር ፀሐይ አሳታሚዎችን ያቋቋመው ዓላማውም ስራዎቻቸው የቀን ብርሃን ሳያዩ ሊቀሩ የሚችሉ ጸሀፍት ተስፋ በመሆን ጽሁፎቻቸውን ማሳተም እንዲችሉ ለማድረግ መዋቅሩን መፍጠር ነበር። በዚህም ያልተገደበ ጥረቱ የኤልያስ ተስፋ ምሁራዊ የሀሳብ ልውውጦች ማህበራዊ ዳኝነት የሚንጸባረቅበትን መድረክ እውን ሆኖ ማየት ነበርና።

ኤልያስ የኢትዮጵያን ባህላዊ እሴቶች ለማሳደግ በሚያደርገው ያልተገደበ ጥረቱ ተወዳዳሪ የሌለው አስደናቂ ውጤቶችን ያስመዘገበ ሆኖ ይገኛል። ኤልያስ ወደ ዩ.ኤስ አሜሪካ የመጣው በመስከረም 1994 (እአአ) ሲሆን አመጣጡም በሚሽጋን ስቴት ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው 12ኛው ዓለምአቀፍ የኢትዮጵያ ጥናቶች ኮንፍረንስ ላይ ለመሳተፍ ነበር።

ብዙም ሳይሰነብት የኢትዮጵያን ሪቪው መጽሔት በማዘጋጀት መጽሔቱ ከህትመት እስከወጣበት 2000 (እአአ) ድረስ ሲሰራ ቆየ። ይህ መጽሔት ከህትመት ከወጣ በኋላ ኤልያስ ጊዜውን ፀሐይ አሳታሚዎችን በማቋቋም ላይ አዋለ። ፀሐይ የሚለው ስምም በ1997 ኢትዮጵያ ውስጥ ያረፉትን እናቱን ለመዘከር የተጠቀመበት ነው። መሰረቱን Loyola Marymount University ያደረገው ፀሐይ አሳታሚዎች ባለፉት 10 ዓመታት ወደ 60 የሚጠጉ በተለያዩ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑ የምርምር እና የስነጽሁፍ ስራዎችን አሳትሞ አቅርቧል። ከእነዚህ ህትመቶቹ ውስጥም አብላጫዎቹ በኢትዮጵያና በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው። ከፀሐይ አሳታሚዎች የሚወጡት የህትመት ውጤቶች ዘርፈ ብዙ የሆኑ የፖለቲካ ይዘት ያሏቸው ሲሆኑ ያለ አንዳች ወገንተኝነትና ሴንሰርሺፕ ነው የሚታተሙት።

በኢትዮጵያና በአፍሪካ ታሪክ፤ ፖለቲካ፣ አንትሮፖሎጂ፣ ኢኮኖሚ፣ ሀይማኖትና ባህል ላይ በማጠንጠን ከታተሙት በርካታ ቀዳሚ የምርምርና ዳግም ህትመቶች መካከል የሚከተሉት ጥቂቶቹ ናቸው: Tradition & Change in Ethiopia (2010), Feudalism and Modernization in Ethiopia (2006), Wit and Wisdom of Ethiopia (1999), Enough with Famines in Ethiopia (2006), The Survival of Ethiopian Independence (2004), A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (2010), A History of the Beta Israel (Falasha) (2010), Protestant & Catholic Missions in Orthodox Ethiopia (2007), Life and Culture in the Townships of Cape Town (2007), AIDS Orphans and their Grandparents (2006), Wax and Gold (2005), Civil Wars and Revolution in the Sudan (2005), Ethiopia in Wartime (2004). የሚሉት ሲገኙበት ፀሐይ አሳታሚዎች ለአደባባይ ያበቃቸውን መጻህፍት ሙሉ ዝርዝር ቀጥሎ ያለውን በመጫን ማግኘት ይችላሉ…

በ2004 (እአአ) ፀሐይ አሳታሚዎች The International Journal of Ethiopian Studies (IJES) በመባል የሚታወቀውን አካል መሰረተ። የዚህ ዓለምአቀፍ ተቋም የጥናት ወረቀቶችንም JSTOR በመባል በሚታወቀው የኦንላይን አካዳሚክ ጆርናልስ ማከማቻ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት ይቻላል። በርካታ ኢትዮጵያዊያን ምሁራንና ተመራማሪዎች እኔን ጨምሮ ፕሮፌሰር ሜይማየር መናሰማይ፣ ወርቁ ነጋስና አሉላ ፓንክረስት IJES በአዘጋጅነት አገልግለናል። IJES የኢትዮጵያዊያንን ተሞክሮ መሰረት አድርጎ በአመት ሁለት ጊዜ እየታተመ የሚወጣ የምርምርና የጥናት ጋዜጣ /ጆርናል/ ነው። በእንግሊዝኛና በአማርኛ የሚታተመው ጋዜጣም የተልእኮው /የአላማ/ መገለጫ እንደሚከተለው ተቀምጧል።

IJES ኢትዮጵያዊያን ምሁራን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ጥናታዊ ሀሳቦቻቸውን የሚያንሸራሽሩበት የጋራ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጅቶላቸዋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ዲሞክራሲን ለማስፈንና የኢኮኖሚ ብልጽግናን ለማምጣት ስር የሰደደ እንቅፋት ሆኖ የሚገኘው የአፍሪካዊያን የእውቀት አድማስ በዘመኑ የማህበራዊ ሳይንስ ላይ ብቻ ጠብቦ እንዲገኝ በመደረጉ ነው። አፍሪካዊያን፣ ኢትዮጵያዊያንንም ጨምሮ ስለ ራሳቸው የሚመረምሩ፣ ሚዛን ላይ የሚያስቀምጡ፣ ስለራሳቸው የሚገመግሙ፣ የገዛ ታሪካቸው አሽከርካሪዎች ራሳቸው ከመሆናቸው ይልቅ በውጪያዊ (አውሮፓዊያንና አሜሪካዊያን) አተረጓጎሞች፣ አገላለጾች፣ ማብራሪያዎች፣ መስፈርቶች ላይ ጥገኛ በመሆን ስለራሳችን ማንነትም ሆነ ስላሉብን ችግሮችና መፍትሄ የምንፈልግ በመሆኑ ነው።”

ፀሐይ አሳታሚዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በርካታ ብሄራዊ ጉባኤዎችን /ኮንፍረንሶች/ ያዘጋጁ ሲሆን ለወጣት ፊልም ሰሪዎችም የፊልም ፌስቲቫል ስፖንሰር አድርጓል። ኤልያስ ለኢትዮጵያዊያን፣ ለአፍሪካዊያንና ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ያበረከተው አስተዋጽኦ ዝርዝር ሰፊ ሲሆን ይህም በእጅጉ ሊያስመሰግነው ይገባል። ኤልያስ ባበረከተው ውጤታማ ተግባር ታላቅ ኩራት የሚሰማን አድናቆታችንን ስንገልጽ ምናልባት አጋናችሁታል ልንባል እንችል ይሆናል። ይሁንና ሌሎች የኤልያስን ያላሰለሰ ጥረት የገመገሙ ይበልጥ ገለልተኛ አስተያየታቸውን ሊሰጡ ይችላሉ።

ከፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ዊንዲ ቢልቸር (Prof. Wendy Belcher) ሲጽፉ “ኤልያስ እጅግ ጠቃሚ የሆነ የተለየ ተግባር እያከናወነ ነው። ከአፍሪካ ክፍለ አህጉር ጥቂት አሳታሚዎች ብቻ ይገኛሉ። በዩ.ኤስ አሜሪካ በአፍሪካዊያን አሳታሚዎች የተያዙና በአፍሪካዊያን ቋንቋ የሚያሳትሙ ቁጥራቸው እጅግ አናሳ ሆኖ ይገኛል። ለኢትዮጵያዊ ደግሞ የራሱ ህትመት መኖሩ ከሌሎች ማህበረሰቦች ይበልጥ አግባብ ይሆናል። አንድም ከ3ሺህ ዘመን በላይ የዘለቀ የጽሀፍ ቋንቋ ያላቸው በመሆኑ ሁለትም ይህንን ጥንታዊ የጽሁፍ ቋንቋ ጠብቆ በማቆየት አንጻር በህትመት ተግባር ውስጥ የኖሩበት በመሆኑ። ኤልያስ የተሰማራውም በዚህ ረዥምና አኩሪ መስመር ላይ ነው።”

እንግዲህ ኤልያስና ፀሐይ አሳታሚዎች የኢትዮጵያንና የአፍሪካን ታሪክና ባህል በመጠበቅ፣ በመንከባከብና አንፀባርቆም እንዲወጣ በማድረግ እተጫወቱ ያሉት ሚና ይህን ይመስላል።

መጽሀፉን /የመንግስቱን/ በህገ ወጥ መንገድ ኮፒ አድርገው በድረ ገጽ የለጠፉት የጥቃት ኢላማቸው ጸሀፊው /መንግስቱ/ ሳይሆን ኤልያስና ፀሐይ አሳታሚዎች ናቸው። በዚህ ወንጀላቸውም እየተቃወሙ ያሉት የኢትዮያዊና አፍሪካዊ ባህል መሰረት ጽንስን ብቻ ሳይሆን ለበርካታ አመታት በምርምር ጊዜያቸውን የሰውትን ምሁራንና ፀሀፊዎችንም ጭምር እንጂ። የዚህ አከራካሪ አልባ ወንጀል ሰለባዎችም መላ ኢት ጵያዊያንና አፍሪካዊያን ናቸው።

ኤልያስ ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ ታላቅ ክብርንና የመንፈስ ኩራትን ያመጣልን መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው። በ2007 (እአአ) የአለም የሰላም ፌደሬሽን እና (Ambassador for Peace by the Universal Peace Federation and the Interreligious and International Federation for  World Peace) የተተባሉት አለማቀፍ ተቋማት በአፍሪካዊያን ምሁራን፣ ገጣሚያን፣ የታሪክ ተመራማሪዎችን፣ አካዳሚያን፣ የስነ ጥበብ አፍቃሪያንና ጋዜጠኞች መካከል የሚካሄድ የውይይት መስመር ለመዘርጋት ኤልያስን የሰላም አምባሳደር አድርገው ሰይመውታል።

በሎስ አንጀለስ ጥቁሮች መካከል ‘ማ ማን ነው?’ (Who’s Who in Black Los Angeles) በሚለው የ 2008 (እአአ) አመታዊ እትም ምረቃ ስማቸው ከተጠቀሰው ስመ ጥር ግለሰቦች ለምሳሌ ከእነ ስቲቭ ዎንደር (Steve Wonder, Tavis Smiley, Kobe Bryant, Isaiah Washington and Dr. Maulana Karenga) ጋር የኤልያስ ስም ቀልሞ ይገኛል። በሳምንታዊው የሎስ አንጀለስ እትም ላይም በሎስ አንጀለስ ከሚገኙት እራሳቸውን ከቻሉት ነጻ ፕሬሶች መካከል በአውራነት ከተጠቀሱት አንዱ ኤልያስ ነው። በተጨማሪም በአሜሪካ ድምጽ በብሄራዊ የህዝብ ራዲዮ፣ በዶቼ ቬላ፣ በኤስ.ቢ.ኤስ አውስትራሊያና በበርካታ ሌሎች መገናኛ ብዙሀን በተለያዩ ባህላዊ ጉዳዮች ላይ ቃለ ምልልስ አድርጓል።

በነጻ ፕሬስ ለምታምኑ ኢትዮጵያዊያን እና ለሌሎችም ሁሉ የቀረበ ልዩ አቤቱታ

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በፀሐይ አሳታሚዎች ላይ በተፈፀመው የቅጂ መብት ዘረፋ ወንጀል ጎዳና የአሜሪካን ኮንግረስ በሁለት ህጋዊ አማራጮች ላይ ዘክሯል። አንደኛው የህግ መስመር The Preventing Real Online Threats to Economic Creativity and Theft of Intellectual Property Act (“PIPA”) በመባል የሚታወቀው ሲሆን ይህም ህግ ለዩ.ኤስ አሜሪካ ጠቅላይ አቃቢ ህግ በዘረፋ ወንጀል የተሰማራን “ድረገጽ” የማገድ፣ የማዘጋት ድረ ገጹ ለመንቀሳቀስ የተመዘገበበትን ስምና ማእከል የማግኘት መብት ሰጥቶታል። የኦላይንን ዘረፋ ማቆሚያ ደንብ The Stop Online Piracy Act (SOPA) ለዩ.ኤስ ህግ አስፈጻሚዎች ተጨማሪ ህጋዊ አድማስ በመስጠት በአእምሮ ውጤት ስራዎች ላይ በድረ ገጾች የሚፈጸመውን የወንጀል ትራፊክ ለመዝጋት እንዲችሉ ያደርጋቸዋል። ህግ አውጭዎች በተለያዩ የአፈጻጸም ሂደቶች ላይ እልባት እስከሚያገኝ በእኛ በኩል ልንፈጽመው ምንችለው አብይ ነገር ይኖረናል። በኢትዮጵያዊያንና አፍሪካዊያን ዲያስፖራ ነዋሪዎች ውስጥ የሚገኘውን ልዩና መተኪያ የሌለውን ፀሐይ አሳታሚዎች መደገፍና ከጥቃት ተከላክሎ ማቆየት። ከሁሉም በላይ የፕሬስ ነጻነትንና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በማስከበር በጽናት መቆምና መከላከል የሚገባን ጋዜጦችን ከሚያግዱና ማተሚያ ቤቶችን ከሚጠረቅሙ አምባገነን መሪዎች ብቻ ሳይሆን የቅጅ መብት ህግን በሚጥሱና አሳታሚዎችን ለኪሳራ ለመዳረግ ከተሰማሩትም ጭምር ሊሆን ይገባል።

ትክክለኛ ነገር ለማድረግ እንነሳ

የተጻፈውን የወንጀል ተግባር በማወቅም ይሁን ባለማወቅ መጸሀፍን /የመንግስቱ ኃይለማሪያምን/ ወደ ኮምፒውተር መጋዚኖቻችሁ ያደረጋችሁ ወይንም ያተማችሁ  ከኮምፒውተሮቻችሁ ውስጥ መደምሰስ፣ ያተማችሁም ቀዳዳችሁ መጣል ይጠበቅባችኋል።

መጽሀፉን በኦን ላይን ያነበባችሁም የጸሐይ አሳታሚዎችን አግኝቶ ለማዋየት የሞራል ብቃቱ ሊኖራችሁ ይገባል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ልናጣው የማይገባን የፀሐይ አሳታሚዎች ላይ የተሰራውን የቅጅ መብት ጥሰት ወንጀል በጽኑ የማውገዝ የመንፈስ ጥንካሬ ሊኖረን ተገቢ ሲሆን አሳታሚዎቹንም ልንረዳ ይገባናል።

ግለ ማስታወሻ፦ ካለፉት ስድስት አመታት ጀምሮ ሳምንታዊ መጣጥፎቼንና አስተያየቶቼን ስትከታተሉ የቆያችሁ ፀሐይ አሳታሚዎችን ለመርዳት ርዱኝ። ፀሐይ አሳታሚዎች፣፤ ኤልያስ ወንድሙና ተባባሪዎቹ በአመታት ያልታከተ ጥረት ላበረከቱልን የብርሃን ስጦታ (ፀሐይ) ያለኝ እምነትና ድጋፍ ፍጹም ነው። ከፊት ለፊታችን የተጋረጠው ምርጫም ግልጽ ነው። እጆቻችንን አጣጥፈን በመቀመጥ ታሪካችንን፣ ባህላችንንና የነገ እጣችንን ድቅድቅ ጨለማ ሲውጠው መመልከት፤ አልያም በኢትዮጵያችን፣ በአፍሪካችንና እስከ ዓለምም ዳርቻ ፀሐይ እንዳትጠልቅ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እና ፀሐይ አሳታሚዎችን ለመርዳት እንድንችል ልትረዱኝ ትችላላችሁን?

 

ፕሮ/ር አለማየሁ ገብረማሪያም ትርጉም፦ ኢትዮጵያ ዛሬ (ኢዛዝክ)

Share this post

Share on facebook
Share on twitter
Share on linkedin
Share on pinterest
Share on print
Share on email

Recent News

“ኢትዮጵያን ገፍተን ገፍተን ገደሉ ጫፍ እያደረስናት ነው “ኤልያስ ወንድሙ የፀሐይ አሳታሚ መስራችና ስራ አስኪያጅ -ክፍል 2 – ARTS WEG

“ኢትዮጵያን ገፍተን ገፍተን ገደሉ ጫፍ እያደረስናት ነው::” ኤልያስ ወንድሙ የፀሐይ አሳታሚ መስራችና ሥራ አስኪያጅ @Arts Tv World​. ስለወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታዎች ከአርትስ ቲቪ ኃላፊ ከአዜብ ወርቁ