የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት፡- ከማኪያቶው ላይ እየተቀነሰ ገቢ የሚደረገው የዳያስፖራ ትረስት ፈንድ የፈረንጆቹን 2019 አዲስ ዓመት መግቢያ ምክንያት በማድረግ በዛሬው ዕለት ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለፀ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመረጡት የዳያስፖራው ትረስት ፈንድ አድቫይዘሪ ካውንስል አባል አቶ ኤልያስ ወንድሙ ስለትረስት ፈንዱ ገቢ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ ገቢው በትናንትናው ዕለት ከአንድ ነጥብ ከአራት ሚሊዮን ዶላር በላይ ደርሶ ነበር፡፡ በዛሬው ዕለት የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት ምክንያት በማድረግ ይህ አሀዝ ወደ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ዶላር ከፍ እንደሚል ይጠበቃል፡፡
እርሳቸው እንዳሉት፤ የዳያስፖራው ትረስት ፈንድ ሐሳብ ከተጠነሰሰ ቆየት ቢልም በአግባቡ ከተጀመረና ድረ ገጹ ይፋ ከሆነ ግን ሁለት ወር አይሞላም ፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የህዳሴ ግድብ አይነት የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት በመንግሥት ደረጃ ተጀምሮ በነበረበት ወቅት የአሜሪካ የገንዘብ ዝውውርን ህግ ተከትሎ ያልተፈጸመ በመሆኑ መንግሥትን ተጠያቂ እስከ ማድረግ አድርሶት ነበር፡፡ በመሆኑም ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር ሲባል ህግና ሥርዓትን በመከተል ገንዘቡን መሰብሰብ በመፈለጉ ጊዜ ሊወስድ ችሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቦርድ ተቋቁሞ ሥራው በአግባቡ እየሄደ ይገኛል፡፡
‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ብዛት ሦስት ሚሊዮን እየተባለ ይነገር እንጅ ከዛ በላይም ነው ብለን እንገምታለን፡፡›› ያሉት አቶ ኤልያስ፣ ለዚህ ምክንያት ብለው ያቀረቡትም 40 ዓመት ያህል ወደውጭ ሲወጣ የነበረው ኢትዮጵያዊ በርካታ ከመሆኑ በተጨማሪ በውጭ አገር የተወለደውም የዚያኑ ያህል ነው የሚል አስተሳሰብ መኖሩን ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ የተጠራቀመ መንግሥትን ያለማመንም ችግር ቶሎ ከውስጥ ያለመውጣት ሁኔታ እንደነበርም ተናግረዋል፡፡
ሁሉም ዳያስፖራ እንደ አገር ከመንግሥት ጋር ለመሥራት ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰው፣ ላለፉት 40 ዓመታት ስጋትና ፍራቻ ውስጥ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ በአሜሪካ ያሉት ዳያስፖራዎች ጊዜ እንደወሰደባቸው ሁሉ በሌሎች አህጉሮች ያሉትም እንዲሁ ጊዜ የወሰደባቸው ነገሮች እንዳሉም ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም ቶሎ ለውጡን ማየት እንዳልተቻለ አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ሰዓት በአውስትራሊያ፣ አረብ አገሮች እና አፍሪካ ውስጥ ያሉትን አጠናክሮ ለማስኬድ የቦርድ አባላትን የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡ በግለሰብ ደረጃም ኃላፊነቱን በመውሰድ እያደራጁ ያሉ ዳያስፖራዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ለአብነትም በኬንያና በደቡብ አፍሪካ የተለያዩ ስብሰባዎች በጉዳዩ ዙሪያ መደረጋቸውን ገልፀዋል፡፡በኢንስቲትዩት ደረጃ ደግሞ ገና በመጠናከር ላይ ይገኛል፡፡
መንግሥት አገርን የሚያስተዳድረው ዜጎች በሚልኩት ጥቂት ገንዘብ እንዳልሆነም አቶ ኤልያስ ጠቅሰው፣ ጠብታም ያህል ብትሆን እያንዳንዱ ዳያስፖራ የሚያወጣው ገንዘብ ‹‹ኢትዮጵያን እየገነባሁ ነው›› ብሎ እንዲሰማው የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትረስት ፈንዱን አስመልክተው በተናገሩ ማግስት ሁሉም የየበኩሉን በማድረጉ ለውጥ መታየቱን ጠቅሰው፣ ገቢው አንድ ሚሊዮን ዶላር መግባቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ይፋ ሲያደርግም በዳያስፖራው ዘንድ ‹‹ለካ እኛም እንፈልጋለን›› የሚል ስሜት ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡ ዳያስፖራው ከዚህ በላይ ያለገደብ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ጠቅሰው፤ አገር ቤት ያለውን ቀዳዳ ለመድፈን እንደሚተጋም አመልክተዋል፡፡
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአሜሪካ ተገኝተው ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ጋር መወያየታቸው ይታወቃል፡፡ በወቅቱም አንድ ዶላር ከማክያቷቸው ቀንሰው የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ላለባቸው የአገራቸው ልጆች እንዲደርሱ ጥሪ ማድረጋቸውም ይታወሳል፡፡
SOURCE: በአስቴር ኤልያስ: አዲስ ዘመን